ቁልፍ ይዞ ማንኳኳት

ነፋሱ በተጨነቀ ድምፅ ይጮኻል፡፡ እሱ ጮኾ ዛፎቹን ያስጨንቃቸዋል፤ ከወዲያ ወዲህ ያንገላታቸዋል፡፡ በነፋሱ ለቅሶ፣ በዛፎቹ ሁካታ ፀጥታው የተረበሸው ጨለማ ለነፋስ እንዲህ አለው፣ “ምን ሆነኻል? መኝታዬ ላይስ እሾህ የምትነሰንሰው ለምንድነው? ስለምንስ ዝምታዬን እንዳልሰማ ታደርጋለህ?”

ነፋስም ለአንድ አፍታ ቆም ብሎ ጨለማን ተመለከተው፡፡ የባዶነት ግርማ ሞገሱ ቢያስፈራውም ሀሳቡን ለመንቀፍ ወደኋላ አላለም፡፡ “ታዲያ እንዳንተ ‘የሆነውንም ሆኖ፣ የሚሆነውንም እንዲሆን የሚፈቅድ’ መሆን ነበረብኝ?” አለው፡፡

ጨለማ ቀጠለ፣ “መሄጃህ ጠፍቶህ፣ የነፋስነት እጣ-ፈንታህ – የነፍስነት ማንነትህ – በረዥም ገመድ ጠፍንጎህ አስሮህ፣ ከወዲያ ወዲህ ስትወናጨፍ መስሎኝ እንዲህ ለቅሶህን የምታሰማው!”

ከዛፎቹ አንዱ ድምፁን ለሰፊው ጨለማ፣ ለተንቀዥቃዡ ነፋስ እንዲሰማ አድርጎ፣ “በቃ… ዘላለምህን ልትጋደም የተፈጠርክ ጨለማ፣ አንተ ልትጨልም እንደሆንከው ሁሉ እሱም ወደዚያና ወደዚህ ሊቃርም ሆኗል… እኛም በነፋስ ሽውታ ልንወዛወዝ፣ ልንንገላታ ተፈርዶብናል” በማለት ክርክሩን ለመቋጨት ሞከረ፡፡ ክርክሩ ግን በቀላሉ የሚቋጭ እንዳልሆነ ሁሉም አውቀውታል፤ ለዘመናት የቆየ ነውና፡፡

እኔም የእነሱን ወግ እያደመጥኩ ከቤቷ በላይ ባለው ጫካ ውስጥ ሆኜ እሷን ውዴን እጠብቃታለሁ፡፡ እሷ ልታየኝ ስለማትፈልግ እራሴን ከጫካው ደብቄያለሁ፡፡
ያን ዕለት ነው፣ አይቼው የማላውቀውን ገላዋን እየናፈኩ፣ ሁል ጊዜ በሀሳቤ የምስመውን ንፁህ ከንፈሯን እያሰብኩ ሳለ፣ ከኋላዬ “የኔ ፍቅር” በሚል ስሜት ትከሻዬን አንድ ነገር ነካ ያደረገኝ፡፡ “የኔ ፍቅር” መባሉ ብርቅ የሆነበት ውስጤ “ወዬ” ብዬ እንድዞር አዘዘኝ፡፡ ዞርኩኝ፡፡ ድንቅ ነበር፡፡

እርሷ… እንኳን ልትነካኝ፣ እንዳልነካት የምትሸሸኝ … እርሷ፡፡

ሁለመናዬ ሊቀላቀላት ቃጣ፡፡ ግን ዝም ብዬ ተመለከትኳት – አትጠገብም፡፡

“ነገ ማታ እዚሁ ጠብቀኝ — እመጣለሁ” አለችኝ፡፡

ነገ መቼ እንደሆነ ግር ስላለኝ መልስ አልሰጠኋትም፡፡ ሄደች፡፡ የቤቷን መንገድ ይዛ ስትሄድ ከኋላዋ አይቻት የፈገግታዋ ብርሃን ሞቀኝ፡፡

እዚያው እንደቆምኩኝ መሽቶ ነጋ፡፡ ነገ ማታም ሆነ፡፡ ጨለማው አካባቢውን አጨልሞታል፡፡ ምንም እንኳ የነፋሱ ሽውታ፣ የዛፎቹ ጫጫታ፣ የዝናቡ እዥታና የመብረቁ ፉከራ ቢያይልም፤ የጨለማው ፀጥታ በትንሹ ይሰማ ነበር፡፡ አሁንም ቆሜያለሁ — ጨቅይቻለሁ፡፡

ድንገት እያደረግኩት ያለሁት ነገር ሁሉ የተደገመ መሰለኝ፡፡ ከዚህ ቀደምም እንዲሁ እመጣለሁ ብላኝ በዶፍ ዝናብ ውስጥ ስጠብቃት የቆየሁ መሰለኝ፡፡ ይህን ክስተት በርግጥም ከአንድ ጊዜ በላይ ኖሬዋለሁ፡፡ ሆኖም ቃሏን ጠብቃ የመጣችበት ጊዜ ትዝ ሊለኝ አልቻለም፤ ደግሞ ደጋግሞ የሚታወሰኝ የእኔ ቆሞ መቅረት ብቻ ነው፡፡

እናም ሌሊቱ በቆምኩበት ንጋት እንዲሆን አልፈቀድኩም፡፡ የቤቷን መንገድ ይዤ እሷን አገኝ ዘንድ ቀጠልኩ፡፡ ይዘንባል፡፡ ጥቅጥቁን ጨለማ እየሰነጠኩ፣ እሷን ብቻ በህሊናዬ እየሳልኩ ተጓዝኩ፡፡ በጉዞዬም ጨለማው ጨለመኝ፤ ዝናቡ ዘነበብኝ፡፡ ጭቃው “እንዳትሄድ” ብሎ ያዘኝ፤ እኔ ግን “እሄዳለሁ” ብዬ ሄድኩኝ፡፡ ብዙ እሾሆች ወጉኝ፣ ብዙ እሾሆችን ነቀልኩኝ፡፡ ሁሉም ነገር የድካም ነበር፤ ግን ጠነከርኩኝ፡፡ ተጓዝኩኝ — ኖርኩኝ፡፡

ከርቀት ጭላንጭል መብራት ሲታየኝ ተስፋ ብቻ ሆንኩኝ፡፡ ታላቅ ደስታ ተዋሀደኝ፡፡ ፈልገው የሚያልሙት ህልም ሁሉ መሰለኝ፡፡ ወደ መኖሪያዋ ተቃረብኩኝ፡፡

እየተጠጋሁ ስሄድ ግን ሌላ ሆነብኝ፤ አካባቢው ሁሉ ከዚህ በፊት የማውቀው ነበር፡፡ ለካንስ የሚታየኝ የኔው ቤት የመብራት ጭላንጭል ነበር፡፡

አዎን፣ የእሷን የውዴን መኖሪያ አጥቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን የእሷን ቤት ስፈልግ፣ የቤቷን አቅጣጫ ይዤ ስጓዝ እንዴት የኔን መኖሪያ አገኘሁት? ትንግርት ነበር፡፡

እናም አዘንኩኝ፡፡ ነገም ውበቷ ሊርበኝ ነው፤ ሁሌም ፈገግታዋ ሀሳብ ሊሆንብኝ ነው፡፡

የሆነው ሆኗል ብዬ፣ ውስጤን ጊዜያዊ ተስፋ መቁረጥ እንዴት እንደሆን እየነገርኩት፣ በነገ ላይ ተስፋውን እንዲጥል ግን እንዳያመነታ እየመከርኩት ወደ ቤቴ ደጃፍ ተጠጋሁ፡፡

… አሁን ልብ ያላልኩትን ነገር ልብ አልኩ፡፡ እሾህ ሲወጋኝ፣ ዝናብ ሲያረጥበኝ፣ እንቅልፍ ሲያወላክፈኝ ቆይቼ ያጣኋትን ውዴን በሬ ላይ ቆማ አየኋት — እየጠበቀችኝ ነበር፡፡

በዓይኖቿ ብቻ ፈገግ ብላ ተቀበለችኝ፡፡ ትከሻዋ ላይ ጣል ያደረገችውን ጨርቅ አንስታ የረጠበው ራሴን አደረቀችልኝ፡፡ ጉንጬን ሳም አድርጋ፣ “እዛው ብትጠብቀኝ መቼም አታገኘኝም ነበር” አለችኝ፡፡ ከዚያም ደረቷ ስር ወሽቃኝ፣ ሙቀት እየሰጠችኝ ወደ ውስጥ ይዛኝ ገባች፡፡ እኔም ስለ ማንነቷ ትነግረኝ ዘንድ ጠየቅኳት፡፡ ውብ ጡቷን አንተርሳኝ የዘላለም ጥያቄዎቼን ትመልስልኝ ጀመር…

Advertisements

4 Replies to “ቁልፍ ይዞ ማንኳኳት”

  1. i love too much these articles..the way u write, the massage it has, the depth of ur seeing . keep on going.
    i’m curious what kind of books u read..bye bro.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s