ነፃ-ፈቃድ (FREEWILL)

ኑሮዋ ባለመሳካቱ መሳካቱን የምታምን ሴት ብትኖር እናቴ ብቻ ናት፡፡ የለፋችበት ሁሉ ሳይሆንላት ሲቀር፣ “አለፋፌም እኮ እንዳይሆን ነበር፤ ስለዚህ ሆኖልኛል ማለት ነው!” በማለት እራሷን የምታፅናና፣ በመፅናናቷም የደስታ ደሴት ላይ ተቀምጣ የሐሴት ባህርን እየጠለቀች የኑሮ ጥማቷን የምታረካ ብልህ ሴት፡፡ ‹ተመስጌን› ማለትን እንደመተንፈስ አምና የተቀበለችው እናቴ ሁሌም ቢሆን ዛሬን እንዳትራብ ነው ጥረቷ፡፡

በደሴቷ ላይ እየኖረ ደሴቷን የፈጠራት ባህር ያልቅ ይሆን በማለት ከባህሩ እየጠለቀ በደሴቷ ላይ በቆፈረው ጉድጓድ ውሃ የሚያጠራቅመው ደግሞ አባቴ ነው፡፡ ነገ ምን እበላለሁ በማለት ዛሬን ጾሙን የሚያድረው አባቴ አንድ ቀን መኖር እንደሚጀምር የሚያምን ሰው ነው፡፡

እናቴ “ተመስጌን” ብላ፣ ያገኘችውን በልታ ዛሬን ትኖራለች፡፡ አባቴ ደግሞ ያገኘውን ነገን ለመኖር ሲል ሳይበላ ዛሬ በረሀብ ይሞታል፡፡

ታዲያ እኔ ከነኚህ የተለያዩ ስሮች በቅዬ እጣ ፈንታዬ ምን ይሁን? ያለ አባት፣ ጠብ እርግፍ ሳትል፣ ያገኘችውን በልታ… አብልታኝ ያኖረችኝን የናቴን ባህሪይ ልውረስ? ወይንስ የአኗኗር ዘይቤውን እርሱ ሳይነግረኝ ከአሟሟቱ የተረዳሁለትን፣ የ‹ከንቱ› አባቴን ባህሪይ ልካን?

እንደዚህ የህይወት መንገዴን ለመራመድ ሳቅማማ አንድ ነገር ትዝ አለኝ…

ድሮ ድሮ… እኔ እራሴ ወደዚች ዓለም ከመከሰቴ በፊት አንድ ድምፅ እንዲህ አለኝ፣ “በተቀደደልህ ቦይ ትፈስ ዘንድ ሆኗል፡፡”

ይህ ድምፅ ይህንን ብሎ የተናገረኝ በህልሜ ይሁን በእውኔ በትክክል አላስታውስም፡፡ ብቻ ከፊት ለፊቴ ቁጭ ብሏል፡፡ የደፈረሰው ዓይኑ ከተጨራመተው ግምባሩ ጋር ደመናማ ቀን ቢያስመስለውም አያስፈራም፤ ያስጠላል እንጂ፡፡ ምናልባት አስጠልቶ የታየኝ የንግግሩ መልዕክት ሳይሆን አልቀረም፡፡ መልክ ያለው ድምፅ ሲገጥመኝ የመጀመሪያም፣ የመጨረሻም ጊዜ ነበር፡፡ እናም ይህ መልከ-ጥፉ ድምፅ እየደጋገመ፣ “በተቀደደልህ ቦይ ትፈሳለህ” ይለኛል፡፡

የዚህን ድምፅ ሀሳብ ልቀበል ሞክሬ ነበር፡፡ ነገር ግን የተቀደደልኝ ቦይ ሁለት ነበርና በየትኛው እፈስ ዘንድ ጠፋኝ፡፡ አባት እና እናቴ ከሰሩለልኝ መንገዶች አንዱን መምረጡ ራሱ ሌላ ህይወታዊ ጉዞ ሆነብኝ፡፡ እሰከገባኝ ድረስ ደግሞ ወደዚች ዓለም የመጣሁት ለመኖር ነው፡፡ ኑሮም ቢሆን እስካሁን ድረስ እኔን ጠብቆ የኖረው እኔ እንድኖረው ነውና መኖር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡

ያም ሆኖ እስካልኖርኩበት ጊዜ ድረስ የዚያ የጭጋጋማ ድምፅ ንግግር ይከነክነኛል፡፡ ‹እንደተነዳኸው ትጓዛለህ› የሚለኝ በምን ምክንያት ነው? እየተነዱ እንደኖሩት ሁሉ፣ እየመሩ የኖረ እንዳሉ አይውቅምን? ሳይነዱም፣ ሳይመሩም መኖር አይቻልምን? የተነዱትም፣ የመሩትም በገዛ ፈቃዳቸው አልነበረምን? ይህንኑ እየደጋገመ ከሚነግረኝ ምን አለበት ሌላ ነገር ቢለኝ ኖሮ?

በቃ፣ በተብረቀረቀ ብርሃን ተከቦ፣ በሚያሰግድ ግርማ ሞገስ ተውጦ፣ በጠራው ዓይኑ እየተመለከተኝ… “እናት እና አባትህ እኮ ወደዚች ዓለም ትመጣ ዘንድ ምክንያት ሆኑ እንጂ የአንተን ህይወታዊ መንገድ ሰሪ አይደሉም” ቢለኝ ኖሮ ተመኘው፡፡ እንዴት እኖር እንደነበርም ታየኝ፡፡

ግን ደግሞ እርሱ ማነው? ከዘመን ዘመን ሲወራረድ፣ ከባህል ባህል ሲወላለድ የመጣ አንድ ተራ ድምፅ ነው እንጂ በእኔ በግለሰቡ እጣ ፈንታ ላይ ይወስን ዘንድ ማን ሥልጣን ሰጠው፡፡ ምንም ባይነግረኝ ኖሮስ መኖሬ ይቀር ነበር?

ኧረ ይጨንቃል፡፡

ሰው እየኖረ እያለ ለኑሮ ይጨነቃል፤ እኔ ደግሞ እንዴት ብዬ ልኑር በማለት ጥልቅ ሀሳብ ውስጥ ገባሁ፡፡

እረኛው በጎቹን እየነዳ በሄደ ጊዜ ከመሀል አንዷ በግ ‹ወዴት ነው የሚወስደኝ ይኼ እረኛ!› ብላ ብትቆም ‹ወግጅ› ሲል በያዘው ሽመል መንገዷን እንድትቀጥል ያደርጋታል፡፡ እኔ ግን ይህን ያህል ጊዜ ልኑር፣ አልኑር እያልኩ ቆሜ በማሰላስል ሰዓት ‹አርፈህ ኑር!› ያለኝ ማንም የለም፡፡ ታዲያ ይህን ጊዜ ትንሽም ቢሆን ያለመኖር መብት እንዳለኝ ተሰማኝ፡፡

እስካሁን ብዙ ሀሳቦች መጥተውልኝ፣ ብዙ ምኞቶች ተመኝቼ፣ ብዙ ውሳኔዎችን ወስኛለሁ፡፡ ነገር ግን መኖር አልጀመርኩም፡፡ ዛሬ ግን ለወሳኝ ውሳኔ እየተንደረደርኩኝ ነው፡፡

እናቴ ‹ተመስጌን› ባይ፣ አባቴ ደግሞ ‹ተስፈኛ›፡፡

እናቴ ዛሬ ያገኘችውን ቆርጥማ ዘላለም የምትኖር፤ አባቴ ደግሞ ያለውን ለነገ አስቀምጦ ዛሬ ሳይበላ በረሃብ የሞተ፡፡

አባቴ ያለውን ቅሪት ለነገ ሲያስቀምጥ “ያለቺኝ ሀብት ነገ ሚስት አግብቼ ልጆች ስወልድ መተዳደሪያ ትሆነኛለች” ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በተስፋ ሲኖር ይህን የተናገረ ዕለት በረሃብ ሞቷል፡፡ ታዲያ አባቴ እኔን ከእናቴ ከመውለዱ ይቅርና፣ እናቴን ከማወቁ በፊት ሞቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥያቄዬ ሁሉ መልስ አፈለቀልኝ፡፡

ያ ለማየት እንኳን ያስጠላኝ የነበረው ድምፅ ጉሮሮው ይድረቅ እንጂ እኔስ መኖሬንም፣ አለመኖሬንም አቆምኩኝ፡፡ ምክንያቱም በጊዜ የሞተው አባቴ ይመስገን፣ ለካንስ ጭራሹኑ አልተወለድኩም!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s