በግዛው ለገሠ

“ጥርስሽ እንደማታ ጀንበር የውበት ብርሃኑን የሚያፈናጥቀው ተፈጥሮ በስጦታ መልክ ያበረከተችልሽ ውበት እንዳይመስልሽ — መስተዋት ብቻ የሆነው ጥርስሽ የእኔን ወርቃማነት ሲያንፀባርቅ እንጂ!

“ትወጂኛለሽ፣ ደስታን ከእኔ እንጂ በውልደት አላገኘሽውም፡፡ ባየሽኝ ጊዜ በባዶነት የተሞላው ውስጥሽ በጥርስሽ ፈገግ ማለት ብቻ ደስታን መሰብሰብ ይጀምራል፡፡ ፈገግታሽ ያምራል፤ ማማሩ ግን የእኔው ውጤት ነው፤ ከእኔው የመጣ ውበት፡፡

“ለማየት ብቻ የተፈጠረው … ያ እንኳን በአዩኝ አላዩኝ አስተያየቱ የተለመደው… አንቺ ደግሞ እንደ ዋና የብርሃን አፍላቂ ምንጭ አድርገሽ የምታምኚበት ዓይንሽ ከፊት ለፊቱ ባለሁ ጊዜ በቀለም አልባ ገመዱ ከዓይኔ ውስጥ ብርሃንን ይጠቀልልና “ህይወትህን አበራሁልህ” ይለኛል፡፡ እኔን ባላየኝ ጊዜ እኮ መጨፈንና መገለጡ ልዩነት እንደሌለው እራሱ ዓይንሽ ያውቀዋል፡፡

“መኖር ያለ እኔ ላንቺ ምንም እንደሆነ አልተረዳሽም ማለት ነው? ከሰል የነበረው ስሜትሽ ደረቴ ላይ ጋደም እንዳልሽ በደቂቃ ፍም ይሆንብሻል፡፡ በአንገቴ ተሸጉጠሽ ስሜትሽ ፍም እንደሆነው ሁሉ በተለየሁሽ ጊዜ ደግሞ አመድ እንደሚሆን አትጠራጠሪ፡፡

“አውቃለሁ፣ ሁልጊዜም እንደምትወጂኝ ትነግሪኛለሽ፡፡ ነገር ግን ‹እወድሀለሁ› አባባልሽ ‹ብትለየኝ ግን አልሞትም› የሚል መልዕክት እንዳለሁ ያስታውቃል፡፡ ትሰሚኝ እንደሆነ ልንገርሽ፣ እኔን ከማግኘትሽ በፊት ሞተሽ ነበር፤ ብታጪኝም ትሞቻለሽ . . .”

እያልኩ የበላይነቴን ከበታችነቷ ጋር አጣቅሼ በፍቅር ጦር በተሸነቆረው የህይወት ቀዳዳ ውስጥ ልከታት የምዳዳውን እሷን፣ ዛሬ ደግሞ ምን ዕላት ዘንድ ጠፋኝ፡፡

ዛሬም እንደወትሮው በተወድጃለሁ ጥጋቤ ተሞልቼ፣ ተኮፍሼ እየጠበኳት ነው፡፡ ነገር ግን ከቀጠሯችን ሰዓት አስቀድሜ ነበር የደረስኩት፡፡

ስለ እሷ መምጣት ባልጨነቅም ቶሎ ቶሎ ሰዓቴን እመለከታለሁ፡፡ ባትናፍቀኝም እሷን የማየት ጉጉት እንደነበረኝ ቆይቼ ነው ያስተዋልኩት፡፡

ከወዲያ ስትመጣ ሳያት ፊቴን አጥቁሬያለሁ፤ ልቤ ግን እንደዛሬም አላረፈም፡፡

መታለች ግን ፍፁም እሷን አትመስልም፡፡ ድሮ ድሮ አይደለም አይታኝ፣ በአካባቢዋ እንዳለሁ ካወቀች እንኳን የስንቱን ዓይን በሚስብ ፈገግታ የሚሞላው ፊቷ ፍፁም ጨልሟል፡፡

አሁንም እንደተኮሳተርኩ ነኝ፡፡ በውስጤ ግን መምጣቷ እረፍት እንደሰጠኝ ሁሉ መከፋቷ ጭንቀትን አቀበለኝ፡፡ ‹ምን ሆንሽብኝ?› ወይንስ ‹ምናባሽ ሆንሽ?› ልበላት እያልኩ በሀሳቤ ቃላትን እየመረጥኩ ሳለሁ በዓይኖቿ የተከማቸው እምባ እንዳይወርድ እየታገለች በተሰባበረ አንደበት “ግን … ትወደኛለህ?” በማለት ጠጣር ጥያቄ ጠየቀችኝ፡፡

“እወዳታለሁ እንዴ?” እሷ ከጠየቀችኝ ይልቅ እኔው እራሴን የጠየኩት ጥያቄ ከበደኝ፡፡

አሁን ተጠራቅሞ የነበረው እምባዋ ንፁህ ጉንጯን አበስብሶታል፡፡ አልቻልኩም፤ የእኔም እምባ ከገንዳው ሞልቶ እንዳይፈስ አንገቴን ሰበርኩኝ፡፡

ጥያቄው ይደገምልኝ — “እወዳታለሁ እንዴ?”

መልስ — ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም የእርሷ ደስታ እኔን ከማግኘቷ ይምሰለኝ እንጂ ዛሬ ያንን ፍንድቅድቅ ፊቷን፣ ያማረ ፈገግታዋን ባለማየቴ ምን ያህል ደስታዬን እንዳጣሁ እኔ ነኝ የማውቅ፡፡ ዛሬ ብርድ ብርድ ያለኝ እነዚያ ብርሃናማ ዓይኖቿ በእምባ ስለተጋረዱ እንደሆነ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ፡፡

እንደዛሬ ሳትከፋ በፊት እየደጋገመች “እወድሀለሁ እሺ” ስትለኝ፣ እኔ ደግሞ “እሺ” የምላት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ አንድም ቀን “እኔም እወድሻለሁ” ብዬ አላውቅም፡፡

ቆጨኝ፡፡ የተቆጨሁት ግን “እወድሻለሁ” ብያት ስለማላውቅ አይደለም፤ እንደምወዳት እስከዛሬ አለማወቄ ነው፡፡

ዛሬስ ተሸንፌያለሁ፤ እንደተኮሳተርኩኝ እምባዬ መውረድ ጀመረ፡፡

እርሷ ግን መሸነፌን በቃላት እንድገልጽ አልጠበቀችም፡፡ ደረቴ ላይ ተለጥፋ እምባዬን ትጠርግልኝ ጀመር፡፡ እኔም ከዚያን ዕለት ወዲህ የእርሷን እምባ ከመጥረግ ቦዝኜ አላውቅም፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s