“የትየለሌዎቹ”

እነዚያን የለሰለሱ ጉንጮቿን እንድዳብሳቸው ይጠቁመኝና የጨበጥኩትን ቦክስ እንድፈታ ያደርገኛል፡፡ ኋላ መሀሉ ላይ ስርጉድ ያለበትን የግራ ጉንጯን ብዬ ቀኝ እጄን ብሰድ … “የምን መዳበስ ነው… በጥፊ በላት እንጂ!!” ሲለኝ ክው እላለሁ፡፡

ሌላ ጊዜ ደግሞ አፌን አሞጥሙጬ የስድቡን ናዳ ላወርድባት ስቃጣ… “ተው እንጂ ተረጋጋ፣ እነዚህ የሚበሉ ከንፈሮቿን ተመገባቸው” ይለኛል፡፡ እኔም የእርሱን ምክር መስማት አያርመኝ ከንፈሮቼን አሹዬ ከከንፈሮቿ ባስጠጋ… “ኤዲያ ምራቅህን ትፋባት እንጂ…” በማለት ቅዥብርብር ያደርገኛል፡፡

ውስጤ አንዳንዴ ይኸው እንደዚህ ግራ ሲያጋባኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ – ያለ እሱ ማን አለኝ – ሲያፅናናኝ… ብቻ ምን አለፋኝ፣ ውስጤ አንዳንዴ እኔን ይመስለኛል… ግን እንለያያለን — ሁለት ነን፡፡

እናም ዛሬ ቦክስ ከመጨበጥ ማሻሸትን፣ ከመሳደብ መሳምን የለመድኩባትን እርሷን ከመሬት ተነስቶ “ተጣላት” አለኝ፡፡

“እንዴ! ምን ነካህ ውስጤ… እሷ እኮ ማለት ቁራጬ፣ ክፋዬ ናት” ብለው፤ “አትሳሳት፣ እርሷ አካልህ ሳትሆን ጥቀርሻህ ናት፡፡ አንተን ለማንፃት ብሎ ቆሻሻህን ቀርፎ የፈጠራት!” አለ በኩራት ውስጠ ምስጢሩን የሚያውቅ ይመስል፡፡

“ብቸኝነት እንዳይሰማኝ ነው እንጂ የፈጠራት!” እልህ ይዞኛል፡፡

“ለብቸኝነትህማ እኔን ውስጥህን ፈጥሯል” አፍ አፌን እየጠበቀ ተቃራኒ መልስ ይወረውራል፡፡

“እሷ እኮ ማለት አሁን ላለኝ ደስታ ዋናውን ሚና የተጫወተች ግማሽ አካሌ ናት፡፡”

“እሷ እኮ ማለት…

“እሷ እኮ ማለት…

“እሷ እኮ ማለት…” እያልኩኝ አያሌ እሴቶቿን ዘረዘርኩለት፡፡

“ስማ አንተ…” አለኝ ሁለት እጁን ወገቡ ላይ ጨብጦ፣ “ስማ… ከእርሷ ጋር በዋልክ ቁጥር የምታሳየው ሽንፈት አይታይህም? ባላገኘሀት ጊዜ የምታመጣው ናፍቆት የሚሉት በሽታስ? ባጣኻት ጊዜስ የምትሸከመው ትዝታ የሚሉት የስጋ ሳይሆን የነፍስ ነቀርሳ? … ከዚያም አንተንም ሆነ እኔን ውስጥህን የምታሰቃየን ስቃይ ትንሽ ተሰምቶህ አያውቅም?”

ዓይኑን እያጉረጠረጠ የጥያቄ ናዳ አወረደብኝ፡፡ እንደዛሬም እሳት ጎርሶ አይቼው አላውቅም፡፡

በርግጥ እኔና ውስጤ በብዙ ነገሮች ላይ እንቃረናለን፣ እንከራከራለን፡፡ በአብላጫዎቹ ጉዳዮች ላይ ያሸንፈኛል፤ እኔም እጄን እሰጠዋለሁ፡፡ እናም አንዳንዴ ፈሪ፣ አንዳንዴ ደፋር፣ ሌላ ጊዜ ተጠራጣሪ፣ አንድ ቀን ደግሞ የዋህ፣ እንደገና ይሉንኝታ ቢስ፣ ቀጥሎ ሰው አክባሪ፣… ብቻ በፈለገው አቅጣጫ እየመራ የፈለገውን ማንነት እንድይዝ ሲያደርገኝ ቆይቷል፡፡

ሌላው ቀርቶ ልደራደርበት በማይገባኝ፣ ዛሬ እስከመተናነቅ ባደረሰን ጉዳይ፣ የህይወቴ ሁሉ ምስጢር በሆነው፣ በፍቅር ሊያዝብኝ ሲቃጣው እያየሁት ስታገሰው ቆይቻለሁ፡፡

ግን ደግሞ “ፍቅር ተፈጥሮህ ነው፣ ዋጋ አታውጣለት፣ ለድርድርም አታቅርበው፣ ቅድመ ሁኔታ አትጠይቅበት…” እያለ ይመክረኝ የነበረባቸው ጊዜያቶች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡

ታዲያ ውስጤ ወቅት እየጠበቀ ሀሳቡን የሚለዋውጥበት ምክንያት ምንድነው? እርሱም እንደኔ ሌላ ውስጥ አለው እንዴ? እርሱም እንደኔ አቋሙን የሚያስቀያይረው፣ “ውስጤ” የሚለው አካል ይኖረው ይሆን? እንዲህ እያለ የሚቀጥልስ ቢሆን? ‹ውስጠ-ውስጠት› የትየለሌ፣ መጨረሻ የለሽ ቢሆንስ? እኔም እራሴ የሌላ አካል ‹ውስጥ› እሆን እንዴ?

ይሄንን ሁሉ የማሰላስለው፣ እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች እያነሳሁ የምጥለው ብቻዬን ሆኜ ነው፡፡ ምክንያቱም በፍቅር ላይ ያለመደራደርን ምስጢር በደህና ጊዜ ስላስተማረኝ፣ “ያንተን ሀሳብ አልሻም፣ ፍቅርን በተመለከተ መኖር እንጂ ማሰብ አያስፈልገኝም” ብዬ አሰናብቼዋለሁ፡፡

እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ማሰብ አቆምኩ፡፡ ፍቅር ማፍቀርን፣ መኖርን እንጂ ማሰብን አይጠይቅም፡፡ ‹እንደወረደ› መሆንን ይሻል፡፡ ይህን በመሆኔም የህይወት ምስጢሩ ገባኝ፡፡ “ፍቅር እውር ነው” ያሉ ሁሉ እውር መጥፎ መሆኑን ሊያረጋግጡ አይችሉምና!!

Advertisements

One Reply to ““የትየለሌዎቹ””

  1. you describe nicely the inner voice that cause most of our problems and confusion. well u raised like everyone a lot of question about this voice, who is that then who am i, which of these voices am i..the final and authentic answer for this simple questions holds the key of our existence..i guess u know what i am talking about.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s